በ Afa Xonso መማር ማስተማር ዙሪያ የሚያጋጥሙ የአመለካከትና ተያያዥ ችግሮችን በሚመለከት የኮንሶ ዞንና የኮንሶ ምሁራን ማህበር ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የበይነመረብ ውይይት ተካሄደ
- Tegegne Tesfaye
- Apr 7
- 2 min read
በኮንሶ ምሁራን አዘጋጅነት በአፋ ኾንሶ መማር ማስተማር ዙሪያ የሚያጋጥሙ የአመለካከትና ተያያዥ ችግሮች ዙሪያ የማህበሩና የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በበይነመረብ ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት በዘርፉ የካበተ ዕውቀት ያላቸው ዶ/ር ኦንጋዬ ኦዳ እና አቶ ጋሎ አይላቴ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ሰብዓዊ መብታቸው ከመሆንም ባሻገር የመረዳት ችሎታቸው እንዲዳብር ይረዳል ብለዋል። በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት ሥራ ሊሰራበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የኮንሶ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንዱ ቦጋሌ በአፋ ኾንሶ መማር ማስተማር ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን በዝርዝር አብራርተዋል። በመማር ማስተማር ሂደቱ እየተስተዋሉ ያሉ የግብዓት፣ የሰው ኃይል ውስንነትና የግንዛቤ ችግሮችን ለመቅረፍም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ኃላፊው አክለው የመማር ማስተማር ሥራው 4ኛ ክፍል እንደደረሰና በትምህርት ፖሊሲ መሠረት ትምህርቱ እስከ 6ኛ ክፍል እንደሚሰጥ ተናግረው ቋንቋው በአርባ ምንጭ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ መሰጠት እንደሚጀመር አቅጣጫ መቀመጡን አብራርተዋል።
የኮንሶ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰራዊት ዲባባ በበኩላቸው ለቋንቋው ዕድገት የሚረዱ አጋዥ መጻሕፍትን በማዘጋጀት ለቋንቋው ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆኑን ተናግረው ማህበረሰቡና ምሁራን ለቋንቋው ዕድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አማኑኤል ኩሲያ በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር የማህበረሰቡን ህልውና የማስጠበቅ ተግባር በመሆኑ ውይይታችን በቋንቋው መማር ያስፈልጋል አያስፈልግም ወይም ጥቅምና ጉዳት ላይ ሳይሆን በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችና የሚፈቱበት ሁኔታ ላይ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኮንሶ ምሁራን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጉማቾ ኩሴ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮች ላይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትጋት መሥራት እንዳለባቸው ገልጸው በመሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
በውይይቱ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
በአፍ መፍቻ ቋንቋ ልጆች እንዲማሩ የመብትና የመንግሥት የፖሊሲ አቅጣጫ በመሆኑ የክርክር መነሻ ከማድረግ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍና በውጤታማነቱ ላይ ርብርብ መደረግ እንደሚገባም ከስምምነት ተደርሷል።
"ሰላማዊ፣ የተለወጠና የበለፀገ የኮንሶ ማህበረሰብ ለማየት ተግተን እንሰራለን" የኮንሶ ምሁራን ማህበር
🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏🙏
Follow us on
Website:👉
https://www.konsokia.org/
Telegram: 👉https://t.me/konsointellectualassociation2
LinkedIn: 👉https://www.linkedin.com/company/101669921/admin/feed/posts/
Facebook: 👉https://www.facebook.com/profile.php?id=100095004171084&mibextid=ZbWKwL
Tiktok




Comentários